የወንጌል ሚዛኑ
በአሜሪካ ፖለቲካ ምርጫ ሰሞን፣ "ወንጌልን ሚዛናቸው ያደረጉ" ተብለው የሚታወቁ ክፍሎች አሉ። "ኤቫንጄሊካልስ" ይሏቸዋል። ሚዛኑ ምንድነው? ሚዛኑ በዋነኛነት፦ ትዳር ከአንድ ወንድ ከአንድ ሴት ጋር ነው፤ ከትዳር ውጭ የማገጠ፤ ግብረ ሰዶማዊነትን ወይም ግብረ ሰዶምን እና ውርጃን የደገፈ ለአገር መሪነት አይበቃም የሚል ነው። ወንጀል ሲገኝበትስ? ሕፃናትን ከእናት ጉያ ነጥቆ እንደ እንሥሣ በሽቦ አጥር ውስጥ ሲያስርስ? ወንጀል ሳይገኝበት ፣ ስደተኛ ስለ ሆነ ብቻ፣ ነጭ ስላልሆነ ብቻ፣ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረን ሲያንገላታስ? ወንጌል ስለ ስደተኛው ምን ብሏል? ዝም። ይኸ አቋም እርግጥ "ኤቫንጄሊካልስን" በሞላ አይመለከትም። ከወቅቱ ፖለቲካ ጋር እጅና ጓንት ላለመሆን የወሰኑና ዋጋ የከፈሉም አሉባቸውና። ከኤቫንጄሊካልስ ቀንደኛው የቢሊ ግራሃም ልጅ ፍራንክሊን ነው። ፍራንክሊንን አንድ ጋዜጠኛ ቀርቦ ጠየቀው፦ ፕሬዚደንት ክልንተን ከአንዲት ልጁ ከምትሆን ሴት ጋር የማገጠውን መጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀስክ አጥብቀህ በአደባባይ ስትቃወም አልነበርክ? ታዲያ፣ ሦስቴ ፈትቱ፣ ከስንት ሴት ጋር ማግጦ፣ ከፕሬዚደንትነት ውድድር እንዳያሰናክሉት፣ በገንዘብ ብዛትና በጠበቃ ዝም ያሰኛቸው ትረምፕ ሲሆን ምነው ችላ አልክ? የፍራንክሊን ምላሽ፦ የክልንተን ዝሙት ሥልጣን ላይ እያ ለ ነው፤ የትረምፕ፦ ሥልጣን ከመያዙ አስቀድሞ ስለ ሆነ፣ ሥራውን እንዳያከናውን አያግደውም። ይታያችሁ። ኃጢአትን በሥፍራ ሲወስነው! ትረምፕ ኢየሱስን ተመስሎ ታማሚ ሲያክም በማኅበራዊ ሚድያ ታየ። ፍራንክሊን፦ ትረምፕ ሆን ብሎ ይህን አያደርግም፤ ለምን በየሰበቡ ለመውቀስ ታነፈንፋላችሁ? ፍራንክሊን፦ ትረምፕ በወንጌል አምኖአል፤ ነፍሱም ድናለች ይላል። ጋዜጠኛ፣ ትረምፕን...