የወንጌል ሚዛኑ
በአሜሪካ ፖለቲካ ምርጫ ሰሞን፣ "ወንጌልን ሚዛናቸው ያደረጉ" ተብለው የሚታወቁ ክፍሎች አሉ። "ኤቫንጄሊካልስ" ይሏቸዋል። ሚዛኑ ምንድነው? ሚዛኑ በዋነኛነት፦ ትዳር ከአንድ ወንድ ከአንድ ሴት ጋር ነው፤ ከትዳር ውጭ የማገጠ፤ ግብረ ሰዶማዊነትን ወይም ግብረ ሰዶምን እና ውርጃን የደገፈ ለአገር መሪነት አይበቃም የሚል ነው። ወንጀል ሲገኝበትስ? ሕፃናትን ከእናት ጉያ ነጥቆ እንደ እንሥሣ በሽቦ አጥር ውስጥ ሲያስርስ? ወንጀል ሳይገኝበት፣ ስደተኛ ስለ ሆነ ብቻ፣ ነጭ ስላልሆነ ብቻ፣ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረን ሲያንገላታስ? ወንጌል ስለ ስደተኛው ምን ብሏል? ዝም። ይኸ አቋም እርግጥ "ኤቫንጄሊካልስን" በሞላ አይመለከትም። ከወቅቱ ፖለቲካ ጋር እጅና ጓንት ላለመሆን የወሰኑና ዋጋ የከፈሉም አሉባቸውና።
ከኤቫንጄሊካልስ ቀንደኛው የቢሊ ግራሃም ልጅ ፍራንክሊን ነው። ፍራንክሊንን አንድ ጋዜጠኛ ቀርቦ ጠየቀው፦ ፕሬዚደንት ክልንተን ከአንዲት ልጁ ከምትሆን ሴት ጋር የማገጠውን መጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀስክ አጥብቀህ በአደባባይ ስትቃወም አልነበርክ? ታዲያ፣ ሦስቴ ፈትቱ፣ ከስንት ሴት ጋር ማግጦ፣ ከፕሬዚደንትነት ውድድር እንዳያሰናክሉት፣ በገንዘብ ብዛትና በጠበቃ ዝም ያሰኛቸው ትረምፕ ሲሆን ምነው ችላ አልክ?
የፍራንክሊን ምላሽ፦ የክልንተን ዝሙት ሥልጣን ላይ እያ ለ ነው፤ የትረምፕ፦ ሥልጣን ከመያዙ አስቀድሞ ስለ ሆነ፣ ሥራውን እንዳያከናውን አያግደውም። ይታያችሁ። ኃጢአትን በሥፍራ ሲወስነው!
ትረምፕ ኢየሱስን ተመስሎ ታማሚ ሲያክም በማኅበራዊ ሚድያ ታየ። ፍራንክሊን፦ ትረምፕ ሆን ብሎ ይህን አያደርግም፤ ለምን በየሰበቡ ለመውቀስ ታነፈንፋላችሁ?
ፍራንክሊን፦ ትረምፕ በወንጌል አምኖአል፤ ነፍሱም ድናለች ይላል። ጋዜጠኛ፣ ትረምፕን፦ ኃጢአትህን ተናዝዘህ ከእግዚአብሔር ይቅርታ ጠይቀሃል? ትረምፕ፦ ጠይቄ አላውቅም፤ እግዚአብሔርን ይቅርታ መጠየቅ ያለብኝ አይመስለኝም። መጽሐፍ እንዳይወጣው አንድ ጨምሬ ላቊም፦ እግዚአብሔር የሰላም ብቻ ሳይሆን የጦርነት አምላክ፣ የፍቅር ብቻ ሳይሆን የጥላቻም አምላክ ነው? ይህን መልእክት በጌታ ልደት ፕሮግራም ላይ በጦር ሚኒስቴር አዳራሽ ብዙ የአገር መከላከያ ሹማምንት በተገኙበት ሲሰበክ ብትሰሙ ምን ትላላችሁ? ግለ ሰብ "ለዓለም ብርሃን" አይሁድ ነን በሚሉ፦ "የሰላም አለቃ" ሲባልስ?
ኢትዮጵያውያን ወንጌል አማኞችስ ወንጌል ሚዛናችን ነው? እንጃ። እስቲ ዳኙ። ላይ ላዩን እናስመስላለን፤ ውስጥ ውስጡን ግን ዘር በዘር ተከፋፍለናል። ፖለቲካና ኃይማኖት አይቀላቀሉም እንላለን፦ ከጌታ ማእድ ይልቅ የቤተ መንግሥት ማእድ ጥሞናል። እግዚአብሔርን ከመፍራት ይልቅ ሰውን ፈርተናል፤ ዝናን ንዋይን መርጠናል። የክብር ጌታን ሳናከብር ክብር ሽተናል!
ኢትዮጵያውያን፣ ቀላሉን እናወሳስባለን ወይም ውስብስቡን እናቀላለን። ግብረ ሰዶም እና ውርጃ፣ በዋነኛነት የምንነቅፈው ጉዳይ ነው። መቃወማችን ተገቢ ነው። መንግሥትን የሚያስከፋ ቢሆን ኖሮ ግን ዝምታን እንመርጥ ነበር፤ እጸልያለሁ ወይም እግዚአብሔር ይፍረድ ብለን እናልፋለን። መስዋእት የሚያስከፍል ሲሆን ግልጹን በ"መንፈሳዊ" ቃል ሸላልመን እናወሳስባለን።
አሜሪካ ያሉ ወገኖቻችን፤ ውርጃ እና ግብረ ሰዶምን የሚደግፉ ሰይጣን ኮሚዩኒስቶች ዴሞክራቶች ናቸው፤ ሪፐብሊካንስ ክርስቲያኖች ናቸው ብለው ያምናሉ። ለመሳቅ እንኳ አይመችም! መረጃ አይሹም፤ በመረጃ ከሆነ ሁለቱም የተበከሉ ፓርቲዎች ናቸው። በሙስናስ? በዘረኝነትስ? ሁለቱም የተበከሉ ናቸው። ይልቅ ተረት ተረት እንወዳለን፦ ለምሳሌ፦ ዴሞክራቶች ሥልጣን ከያዙ፣ ትምህርት ቤቶች ወንዱን ሴት አድርገው ይመልሱባችኋል ዓይነት ተረት!
በዚህ ብቻ ቢያበቃስ? ወንጌላውያን መሪዎች፣ ከተቀደሰው የጌታ ቤት መድረክ ላይ ቆመው፣ ምእመን ማንን መምረጥ እንዳለበት ያስታውቃሉ። እግዚአብሔር እንዲባርካችሁ ከፈለጋችሁ . . . ይላሉ። ኃላፊነታቸው፣ ሐሰቱን መግለጥ፣ የእውነትን ቃል ማስተማር ነው። ምእመን ከኅሊናውና ከወዳጆቹ ተማክሮ፣ በገባው መጠን መዝኖ መምረጥ ፈንታው ነው። ስደተኛን የሚያጎሳቊለውን፣ የጤና እና የመኖሪያ መብት የሚነፍገውን አመራር መደገፍ በራስ ላይ መፍረድ እንደ ሆነ ካልተገነዘበ ቂል ነው። ብዙዎች ሳያስቡበት ተታልለው፣ መንፈሳዊ የሆኑ መስሏቸው ተጎድተዋል፤ ወገኖቻቸውን ጎድተዋል።
አንዳንዶች ወንጌላውያን መሪዎቻችን በዚህም በዚያም የንዋይ ተጠቃሚ ሆነዋል ብለን ለሌላ ቀን እናሳድረው።
ዘመኑን እንደ መዋጀት፣ በተመሳሰልነው መጠን በዓለም ዘንድ አንታመንም። ካልታመንን፣ የያዝነውን ወንጌል የሚያምንልን ማነው? ወንጌል፦ የመስቀሉ ጠላቶች፤ ያልታመኑ ምስክሮች ይለናል!
Comments
Post a Comment