የምስጋና ቀን

ሰሞኑን በአሜሪካ ኖቬምበር 26 ሐሙስ "የምስጋና ቀን" በአገሪቱ በሞላ ይከበራል። ቤተ ሰብ የሚሰባሰብበት እለት ነው። አብሮ የሚበላበትና የሚዝናናበት ቀን ነው። ከያለበት ይሰባሰባል። በመኪና በአውሮፕላን ይጓጓዛል። እንደ አገራችን ዶሮ ወጥ፣ በእለቱ የተለመደው የተኪኒ ሥጋ ነው። 

ክብረ በዓሉ የተመሠረተበትን መቃኘት ይጠቅማል። በፕሬዚደንት አብራሃም ሊንከን ዘመነ መንግሥት ኦክቶበር 3/1863 ዓም፣ በኖቬምበር ወር የመጨረሻው ሐሙስ የምስጋና ቀን እንዲከበር በሕግ ፀና። የሚገርመው፦ ወቅቱ አገር በጦርነት ተዘፍቃ፣ ተመልሶ አንድ መሆን ባጠረጠረበት ወቅት በዓሉ መታወጁ ነው፦ ከወዲያ ያለህ፣ ከወዲህም እግዚአብሔር የምትበላውን አላሳጣህም።  መሐሪ ነውና፣ እንደ በደላችን አልከፈለንም። በዐመፀኝነታችን ምክንያት ምድሪቱ ብዙዎችን ያለ አባት፣ ያለ ባል አስቀርቷል። እግዚአብሔር ይቅር እንዲለን እንማጸነው። ይኸው፣ እልቂቱ ቆሞ፣ አገርም ሳትበተን 162 ዓመት ተከበረ።

ኢትዮጵያውያን (ኤርትራውያን) አመስጋኝ ሕዝብ ነን? እግዚአብሔርን አመስጋኝ ነን? እርስበርስ አመስጋኝ ነን?  አመስጋኝነታችን በክልል አጥረነው ራሳችንንና ሌሎችን፣ ይልቁን ደግሞ፣ እንደ ዐመፀኝነታችን ሳይሆን ምሕረት ያደረገልንን እግዚአብሔርን በድለነው ይሆን? 

አንድን ሕዝብ የሚያለሙት፣ ተስፋ የሚሰጡት ማኅበራዊ እሴቶች አሉ። መገፋፋት መናናቅ ሳይሆን እርስበርስ መከባበር። ስግብግብነት ሳይሆን እርካታ። መራራነት ሳይሆን ደስተኛነት። አለመተማመን ሳይሆን መተማመን። ይኸ በግለ ሰቦች ጤና ላይ እና በአገር ልማት ላይ ትልቅ አስተዋጽዖ አለው። 

ከዚህ ቀደም በሌላ ሥፍራ እንዳመለከትኩት፣ በኢትዮጵያ (ኤርትራ) ማታለል ጥበብ፣ ትእቢት ጀግንነት የተደረገበት ምድር ነው። ያለፈው መራራነት ዛሬን እንዳንኖርበት፣ ነገን በተስፋ እንዳንጠባበቅ አድርጎናል። 

ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ፣ ህወሓት/ሃይለማርያም ደሳለኝ የጳጉሜን ቀናት፦ የእውቀት የማንበብ የፍቅር የሰላም የደስታ ወዘተ ብለው ሕዝብ ከፊቱ ያለውን ጭለማ ዓመት ለማረሳሳት ሞክረው ነበር። ቅንነት የጎደለው ነው፤ እውነታን ክዶ ለማስካደ የተደረገ ሙከራ ነው። ውጤቱ፦ የባሰ አለመተማመን ነበር። የዐቢይ አስተዳደርም ቀጥሎበታል። እንደ ቀደሙት ያታልላል። ሁሌ በጠብ መንገድ ላይ ነው። ያመኻኛል፦ እኔ ሰላም ፈላጊ ነኝ ይላል። ዘወር ብሎ፣ በጠብ ከመጣህብኝ አትችለኝም፤ እንደ አባቶቼ ጀግና ነኝ ይላል።

ኢትዮጵያውያን (ኤርትራውያን) አመስጋኝ ሕዝብ ነን? ተስፋችን የበራ ወይስ የጨለመብን ነው? የስደተኛው ብዛት ሰው በአገር የቀረ አይመስልም። የትምህርት ቤቶች ጥራት መውደቅ፣ የተማረው አገር የሚመራው፣ እውቀት ሳይገበይ፣ ልምድ ሳያካብት፣ በወረቀት ጋጋታ፣ በስም ብቻ አገር ልምራ ብሏል።  

አብሮ፣ ያለውን ተጋርቶ መኖር ሲቻል፣ ጠብና መጋደልን መርጠናል። በትናንቱ ላይ ተጣብቀን ዛሬን መኖር ተስኖናል። ፈቃዳችንን ለማስፈጸም ሕዝብ መጎሳቆሉን መርጠናል። መጋደል ሥልጣን ለመያዝ ነው። መጋደል ቂምና በቀል እንደሚያስከትል ከአሁኑ ታሪካችን መማር አልቻልንም። 

ተስፋ ያለው ሕዝብ ከሞት ይሸሻል። ተስፋ ያጣ ሌላውንም ተስፋ ይነሳል። አመስጋኝነት በጤና ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። አመስጋኞች፣ ባላቸው የሚረኩ ሰዎች፣ ሰውን አክባሪዎች፤ ይልቁን ደግሞ እግዚአብሔርን ፈሪዎች፦ ከማያመሰግኑ፣ ባላቸው ከማይረኩ፣ ሰውን ከማያከብሩ፣ እግዚአብሔርን ከማይፈሩ በበለጠ የጤና እክል ይበዛባቸዋል፤ እድሜአቸው ያጠረ ነው። 

እንደ አገር እንደ ሕዝብ እንደ አገር መሪ ምርጫ ቀርቦልናል። ምርጫችን ይመራናል። ምርጫችን ያኖረናል ወይም ያጠፋናል። 

Comments

Popular posts from this blog

Band of Armenian Orphans

BEING THE PEOPLE OF GOD

Home of the Shy

"Mullah Omar" Is A Farce

ዱቄቱን አምጪው