አማርኛ
Shared with Your frienበእንግሊዝኛ ወይስ በአማርኛ
Ethiopian Church Journal ኖቬምበር 25/2023 ፌስቡክ ላይ ከለጠፈው ዳግመኛ የታተመ።
በእንግሊዝኛ ወይስ በአማርኛ?
ዶ/ር ቼፕኪሩኢ ባሲሊዮ የተሰኘ (ኬንያዊ?) የጠ/ሚ ዐቢይን እንግሊዝኛ ጥራት አናንቆ በትዊተር ገጹ ላይ ከታች እንደ ተመለከተው ከሁለት ቀን በፊት ለጥፏል። አንዳንድ ተቺዎች እንደሚያጋንኑት ይኸ እንደ ጉድ ሊታይ አይገባም፤ መፍትሔው ቀላል ነው። ዐቢይ በአማርኛ አሳባቸውን ይግለጹ፤ ብቃት ያላቸው አስተርጓሚዎች አብረዋቸው ይጓዙ (ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች በቂ አስተርጓሚ አላቸው) ።
በእንግሊዝኛ አጥርቶ መናገር ጠቃሚ ቢሆንም፣ አለመናገር ብዙ ለውጥ አያመጣም። ቋንቋውን እየተረዱም በቋንቋቸው እንጂ የማይናገሩ የአገር መሪዎች ነበሩ፣ ዛሬም አሉ፦ የራሽያው ፑቲን፣ የቻይናው ሺ፣ የዐረብ አገር መሪዎች፣ የፈረንሳዩ ማክሮ፣ የደቡብ አሜሪካ መሪዎች፣ ወዘተ።
አፄ ኃይለሥላሴ ፈረንሳይኛ አጥርተው ይሰሙ ይናገሩ ነበር፤ የአገራቸውን ክብር ለማስጠበቅ ግን አስተርጓሚ ይጠቀሙ ነበር። መንግሥቱ ኃይለማርያም እንግሊዝኛ ይሰሙ ይናገሩ ነበር፤ ብዙ ቋንቋዎችን የሚያውቅ አስተርጓሚ አብሯቸው ይጓዝ ነበር። መለስ ዜናዊ የእንግሊዝኛቸው ጥራት እና የምዕራቡ ባህል እውቀታቸው እንከን አይወጣለትም ብለን እንለፈው።
በየትኛውም ቋንቋ ይነገር፣ ትኲረቱ አቋምን አሳማኝ፣ ለዛና ዘይቤ በተላበሰ መንገድ ለአድማጭ ማስተላለፍ መቻል ነው። አድማጭ ግራ ከገባው ለተናጋሪው (ተናጋሪው ለሚወክለው አቋምና አገር) አክብሮት አይኖረውም። ዐቢይ ከዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ባንጋ ጋር እና በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ በተካሄደው ፓሪስ ኮንፈረንስ ላይ ችግር ገጥሟቸው እንደ ነበረ እናስታውሳለን።
በቋንቋ አለመግባባት ጠብ ሊያስከትል ሁሉ ይችላል! ከኢጣልያ ጋር በ1881 ዓም የተደረገው ውጫሌ ውል ከስድስት ዓመት በኋላ የዐድዋ ጦርነት እንዳስነሳ ትዝ ይበለን፤ ምክንያቱ በእንግሊዝኛ እና በአማርኛ የተፃፈው ሰነድ በአተረጓጎም አለመስማማት ነው። ይኸ የግል ጉዳይ አይደለም፤ የአገር ጉዳይ ነው፤ ሕዝብን በአግባብ የመወከል ጉዳይ ነው፤ አሳብን ተረድቶ የማስረዳት ጉዳይ ነው።
ሁለተኛ፣ ጠ/ሚ ዐቢይ በዓለም አቀፍ መድረኮችና በፓርላማ ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ በቂ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ ንግግሮቻቸው በቂ ጥናትና ምክክር የተጣራ መረጃ ሊገኝባቸው ይገባል። በዘፈቀደ መሆን የለበትም። ለዚህ ነው ብቃት ያላቸው አማካሪዎች መኖር ያስፈለገው። ማማከር ልኩን ሳያለባብሱ በቅንነት ማስረዳት ላይ ነው። የሚ/ሩ አመራር እስከ ዛሬ ከግራ ከቀኝና ከመሓል የሚነሱ ግራ መጋባቶችን ወደ መፍትሔ ማቃረብ ያልተቻለው፣ እያድበሰበሰ ማለፍ፣ ከሕዝብ መደበቅ ያበዛው፣ በዋነኛነት ትክክለኛ አማካሪ አለመኖር ወይም ምክር ካለመቀበል ነው! የሚ/ሩ ንግግሮች እርስ በርስ መጣረስ በቂ ዝግጅት አለመደረጉን ያሳያል! ይኸ መታረም ይኖርበታል።
ሚ/ሩ ብቻቸውን በግላቸው የሚያካሄዱት ዲፕሎማሲ (ከኤርትራው ኢሳይያስ፣ ከግብጽ፣ ከሱማልያ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኢመሬቶች፣ ከፈረንሳይ፣ ወዘተ መሪዎች ጋር) ሌላኛው አሳሳቢ ነገር ነው። ዲፕሎማሲ ብዙ ጥንቃቄ ይሻል። ጥንቃቄ አለማድረግ አለመታመንን፣ ጥርጣሬን፣ መገለል እና መናቅን ያስከትላል። ከላይ እንዳልኩት ይኸ የግል ጉዳይ አይደለም፤ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ነው። አገር እና ሕዝብ ደግሞ ከግለ ሰብ እና ከግል ፍላጎት ይቀድማሉ።
ሦስተኛ፣ ከብልጽግና ፓርቲ ሌላ ሌሎች አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ተደራጅተው በአገራቸው ጉዳይ እንዲሳተፉ እንቅፋት አለማኖር ነው። የፖለቲካ አውታሩን ማስፋት ነው። ኅብረ ብሔር ፖለቲካ ይህንን ይሻል! ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ ነው። "መልካም ምክር ከሌለ ዘንድ ሕዝብ ይወድቃል፤ በመካሮች ብዛት ግን ደኅንነት ይሆናል" (ምሳሌ 11፡14)። ይኸ ክፍል ቅንነት፣ ልበ ሰፊነት እና ትኅትናን ይጠይቃል። ቅን እና አስተዋይ መሪ ራሱን አያስቀድምም፤ ሳይፈራ፣ ሳይታክት፣ ለታቀደው መርሃ ግብር እንቅፋቱ እኔ እሆንን? ብሎ ይጠይቃል። ያለእርሱም እንኳ ቢሆን የታቀደው መሳካቱን ያስቀድማል! መሪነት መስዋእትነት ይጠይቃል የሚባለው ስለዚህ ነው።
ደጋግመን ያየነው ትልቁ አገራዊ ስህተት፣ ከአፄ ኃይለሥላሴ በኋላ የተነሡት ሁላቸውም (መንግሥቱ፣ መለስ፣ ዐቢይ) ያለእነርሱ ራእይ እና አመራር አገር የትም አትደርስም ብለው ማሰባቸው ነው! መንግሥቱና መለስ አደርሳችኋለሁ ወዳሉን ሰላም እኩልነት ብልጽግና ሳያደርሱን በሽሽት እና በሞት ጥለውን ሄደዋል! ቃል የገቡትን ሳይፈጽሙ የቀሩት፦ ብቻቸውን ማድረግ ስላሰቡ፣ ሕዝቡን እንደሚገባ ስላላሳተፉ፣ የሌሎች ዜጎችን ራእይ ስለ ናቁ፣ እነርሱ በሌሉበት አገራዊ አጀንዳ ቀጣይነት እንዲያገኝ ተተኪ ስላላዘጋጁ ነው!
በተለይ አገራችን በኢኮኖሚ አፋፍና በከፍተኛ ሕዝባዊና ተፈጥሮአዊ ነውጥ ውስጥ በምትገኝበት በዚህ ሰዓት፣ እውነታን ወደ ጎን አድርጎ፣ በልጽገናል፣ ከፍታ ላይ ልንደርስ ነው ማለት ክህደት፣ ማታለል፣ አለመታመን ነው። ራእዩ ከመነሻው ስህተት እንደ ሆነስ? ተጋንኖ እንደ ሆነስ? እርምት ያሻው እንደ ሆነስ?
ወንጌል አምነናል የምንል ከእውነት ጋር መቆምን ለድርድር አናቅርብ፤ ይኸማ ኢየሱስን እና ወንጌሉን መቃወም ነው። ይልቅ፣ እውነቱን በማወቅና በማሳወቅ እንትጋ። እግዚአብሔርን መፍራትን ሰው በመፍራት አንተካ! በጌታ ቃል፣ በቅዱሳን ምክክር እና በመንፈስ ቅዱስ ማስተዋል ባልተፈተነ የምኞት ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ እንጠንቀቅ! ከሁሉ በፊት ለመሪዎቻችን፣ ለምድሪቷና ለሕዝቧ እንጸልይ!
Comments
Post a Comment