ወሬ

10 Surprising Facts About Ethiopia | Intrepid Travel Blog 

ድሮን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ግቢ ላይ ተተኩሶ 2 ሰዎች ሞቱ የሚል ዜና ባለፈው ሳምንት ተሰምቶ ነበር። የ ዐቢይ አስተዳደር ምላሽ ምን ነበር? ዝም።

ከሁለት ቀናት በፊት አዲሳባ በድሮን ተመታች የሚል ዜና ተጨምሮ ተናፈሰ። የኢትዮጵያ መሪ ምላሽ ምን ነበር? ዝም።

እርግጥ፣ ያልተመዘገበ ድሮን ጨርሶ እንዳይበርር ትእዛዝ አውጥቷል። የኤርትራን ቆንስላ ዘግቷል። የግብፅን ዲፕሎማት አባርሯል። ለኢትዮጵያ በጎ አስበው የማያውቁ ሁለቱ ወዳጆች አፃፋውን መልሰዋል።

የ ዐቢይ አስተዳደር ባለፈውም ባሁኑም ጦርነት ያላወቀበት ጉዳይ የሕዝብን አመኔታና የዓለም ማኅበረ ሰብን አስተያየት እንዴት መማረክ እንደሚቻል ነው። ዝምታ ወርቅ አይደለም። የሰው ልብ የሚያምነው የተነዛው ወሬ እውነት አለመሆኑን አይደለም። የሰሚ ልብ የሚሰማው፦ ከትንሿ ኤርትራ በሕዝብ ቊጥርና በሃብት ክምችት እጅግ የምትበልጠው ኢትዮጵያ አቅመ ቢስ ሆና መታየቷን ነው። ዐቢይ ይህን ዋነኛ ቊምነገር ካለፈው ስሕተት ተምረው ዛሬም ለይተው አላወቁም።

በደፈናው ብቻ በድንፋታ፦ እኛ እኮ 130 ሚሊዮን ሕዝብ አለን ይላሉ። ወይም፦ ከመቶ በላይ የጦር አውሮፕላኖች። ማንም አይበግረንም። ይሞክረንና ያገኛታል ዓይነት ፉከራ። ጉዳዩ ግን የዓለም ማኅበረ ሰብን አእምሮ ማ ረታ ነው።

ከሁሉ የሚብሰው ግን። የኢትዮጵያን ሕዝብ አመኔታ ማጣት ነው። ሕዝቡ ኑሮ እጅግ መርሮታል። አጥነቱን የሚግጡትን ወሮበሎች ዐቢይ ንክች ማድረግ አልፈለጉም፤ አልቻሉም። ምክንያቱ፣ ወሮበሎቹ የብልጽግና ፓርቲ አባላት ናቸው። 

የአፄ ኃይለሥላሴም የ መንግሥቱ ኃይለማርያምም የ መለስ ዜናዊም መንግሥት የፈረሰው የሕዝብ ልብ ስለ ከዳው ነው።

የዐቢይ ብልጽግና አሸሼ ገዳዎ፣ ልብስ እንጀራ ህክምና መኖሪያ ሥራ መሆን አልቻለም። እንዲያው በድፍኑ ወደ ፊት ጠብቁኝ፤ እያንዳንዳችሁን ቢሊየነር አደርጋችኋለሁ ነው (ቃላቸውን መጥቀሴ ነው)። በሌላ አነጋገር፣ የዜጋ ሞራል ከወደቀ፣ ስጋት ከገባው፣ "አካታች" እና "ጽምዶ" በሚል ስም ግብጽና ኤርትራ ያሠማሯቸው ሆድ አደሮች (በ1983 በኢሕአዴግ ስያሜ እንዳደረጉት)፤ አማራም ኦሮሞም ትግራዋይም ሕዝብ ያልወከላቸው፣ የልብ ልብ ይሰማቸዋል።

ፍርሓት የገባውን ልብ ከማረጋጋት ይልቅ፣ አስቀድሞ ፍርሓት ሳይገባው መተማመኑን ማጠንከር ይቀላል።

የአሜሪካ ዴሞክራቶች፦ አንድ በሉ እንጂ ኢትዮጵያ እንደገና በትግራይ ሕዝብ ላይ ሌላ እልቂት ሳትፈጽም እያሉ ነው። አውሮጳ ያሉ ከነ ተላላኪዎች ተከራዮቻቸው ይህንኑ እያስተጋቡ ነው። ዐቢይስ? ዝም። አምባሳደር አድርገው የሾሟቸው ብዙዎቹ በእንግሊዝኛ ዲፕሎማሲያዊ መግለጫ መስጠት ቀርቶ በአግባቡ እንዴት አደርክ ማለት የማይችሉ ዓይነቶች ናቸው። አንድ ሁለት ቢገኙ፣ ከጠ/ሚ ጽ/ቤት ሳያስፈቅዱ ምንም ማለት አይችሉም። እነ ከተማ ይፍሩ፣ ምናሴ ኃይሌ፣ ጎሹ ወልዴ ረገሙን ይሆን?

ኢሳይያስ አፈወርቂ፣ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከማወጅ ውጭ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ተስማምተው ምነው ለኤርትራ ሕዝብ ልማት አልተጉም? 33 ዓመት ሙሉ ለጦርነት ዝግጅት ነው ወይም ከጦርነት መልስ ነው። ጦርነቱ የሚጠቅመው ለሥልጣናቸው ማስጠበቂያ ይሆን? ሦስት ትውልድ ያለጦርነት በቀር የሚያውቀው የለውም። ይኸ እኔ የምመልሰው ጥያቄ አይደለም።

ሰላም ለምድራችን፤ ሰላም ለኤርትራ ሕዝብ።

Comments

Popular posts from this blog

HaileSelassie's Band of Armenian Orphans

Blue Revolution

መስቀል ዘር የለውም

የዐቢይ ወይስ የዓለም ጦርነት

Dust In The Wind