የዐቢይ ወይስ የዓለም ጦርነት

 


የዛሬው ርእሰ ዜና፣ ህወሓት የመቀሌን አውሮፕላን ማረፊያ ተቆጣጠረ ይላል። እስከምናውቀው ድረስ ህወሓት የክልሉ አስተዳዳሪ ነው። የራሱ የክልል ወታደሮች አሉት። መቀሌ የትግራይ ዋና ከተማ ነው። አውሮፕላን ማረፊያውን ተቆጣጠሩ የተባሉት ከዚያው እንጂ ከውጭ የመጡ አይደሉም። ይኸ ለምን እና እንዴት ዜና እንደ ሆነ አልገባንም። 

ሁለተኛ፣ የዜና አውታሮች ከላይ በስተ ቀኝ የሚታየውን ፎቶ ለጥፈዋል። የሚገርመው ይኸው ፎቶ በፈረንጆች 2024 (ከሁለት ዓመት በፊት) የኦሮሞ "ነፃ አውጭ" ታጋዮች ተሰኝቶ በስካንዲኔቭያ ጋዜጣ ላይ ተለጥፎ ነበር። ያው የተለመደው የፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ መሆኑ ነው። አውሮጳውያን አሜሪካውያን ማ ማ እንደ ሆንን ለይተው አያውቁንም፣ ስንተላለቅ ብንውል ደንታ አይሰጣቸውም። በግርግር አስታራቂ ሆነው ከች ይላሉ፤ ጓዳችንን ይበረብራሉ። በየአንጃችን ቃል ይገቡልናል። በእኛው ኑሮ ያጫርቱናል፤ ይበዘብዙናል። 

ዐቢይ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ፣ እንደ አዲሳባ ነቢያት ቀኝና ግራቸው ያልታወቁ ብዙ ቃላት ያዥጎደጉዱልናል። "ምድራዊ ኃይል" አይቋቋመኝም ብለው ነበር። ሌላም ብዙ ብዙ። ከብልጽግና ፓርቲ ሌላ፣ ከእኔ ሌላ አይታሰብም ብለዋል። በአደባባይ በፓርላማቸው ስብሰባ። ሄዳችሁ አድምጡ። ባጭሩ፣ ዐቢይ ያገራችንን ችግር ከሌሎች ጋር ተስማምተው መፍታት አልሆነላቸውም። "ምክክር ምክክር" ስንል የከረምነው፣ መቋጫ ሳያገኝ አፋፍ ላይ ደርሶ ነበር። በዚህ በአዲሱ ግርግር ገደል ሊገባ ነው። ባለፈው ጊዜ፣ አገራዊ ምርጫ የተላለፈው በዚሁ ሳብያ እንደ ሆነ አይረሳንም።

ደብረጽዮን እና ዐቢይ ይመሳሰላሉ። ዐቢይ ያለእርሳቸው ኢትዮጵያን የሚመራት የተቀባ ግለ ሰብ የለም ብለው ያምናሉ። ደብረጽዮን ከህወሓት ሌላ ኢትዮጵያን ለመምራት የተቀባ ዘር የለም ባይ ነው። አሁን ደግሞ ከኦሮሞ ከአማራ ጋር ግንባር ፈጥረናል እያለ ነው። ሰባት ቡድን ያጣመረ፤ ታስሮ እንደ ተፈታ ሰባት አጋንንት! ደም ካላፈሰሱ አያሳርፋቸውም። 

የሚገርመው የኤርትራ እጅ ከመጋረጃው በስተጀርባ ሾልኮ መታየቱ ነው (ቀላቢዋ ግብፅ ነች)። ኢሳይያስ (ወይም ኢሱ፣ "ዐቢቹ" ቀለበት በምሽት ሆቴል ውስጥ ያጠለቁለት ሰውዬ። ደግሞ የ ሲሲን ቀለበት አጥልቋል)። 

ኢሳይያስ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ቅኝ አገዛዝ ነፃ አወጣሁ ካለ ጊዜ ጀምሮ 33 ዓመት ሙሉ ነፃ ለወጣው ሕዝብ ከጥይት ከጦርነት በስተቀረ ምን እህል ሠፍሯል? ስደት፤ ሥራ አጥነት፤ ስጋት ዘርቷል። ተስፋ የሌለው የባከነ ሕይወት። ወይ ለጦርነት መዘጋጀት ነው ወይም ከጦርነት መልስ ነው። ለሕዝብ የገደደው መሪ፣ ከጦርነት ይልቅ ሰላምና መግባባትን ያስቀድማል፤ በመስጠትና በመቀበል የሚበጀውን ሥራ ይሠራል። ታዲያስ? ኢሱ እርሳቸው የበላይነቱን ካልያዙ አይመቻቸውም፤ የበላይነቱን እምቢ ያለን እረፍት ይነሳሉ። ለኢትዮጵያ የ50 ዓመት የቤት ሥራ እሠጣታለሁ ብለው ዝተው ነበር። እነሆ፣ ሃምሳ ዓመቱ ተቆጥሮ የእርሳቸው እድሜ መቋጫ ላይ ደርሰናል። እስከ ሞት ድረስ ጥላቻ ይኸ ነው።  

ኤርትራ 3 ሚሊዮን ሕዝብ (የኢትዮጵያ ሕዝብ 130 ሚሊዮን፤ የኢትዮጵያ ቆዳ ስፋት የኤርትራን 10 እጥፍ) ይዘው ኢሱ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት አይበቃኝም፤ አየር መንገዱን መጋራት አለብኝ! ከዚህ ቀደም መለስ ዜናዊን ናቅፋ በኢትዮጵያ መገበያያ ይደረግ ብለው አዝዘውት ነበር፤ ብልሓተኛው መለስ፣ ጨርሶ አይታሰብም ብለው። ታላቅ ወንድማቸውን ኢሱን ሃያ ዓመት ከዓለም ማኅበረ ሰብ አግልለው ዘግተውባቸው ነበር (ዐቢይ በአሜሪካ ትእዛዝ፣ በኖቤል ሰላም ሽልማት አግባብተው፣ ለኢሱ ደጁን ከፍተውላቸዋል)። ያ ሁሉ ግርግር ያ ሁሉ ፍከራ ሐተታ የት ገባ? ለምን ባጭር ቀረ? የኢሳይያስን እናውቃለን። የዐቢይ ምላሽ ምንድነው? ወይስ አይጠየቁም?

አሁን ሰባት ሆነው የተነሡት "አካታች" ቡድኖች በቀደም እለት አይነጋገሩም ነበር፤ ዓይንህን ላፈር ይባባሉ ነበር። አሁን ምን ነገር ተገኘና ነው ፍቅረኞች የሆኑት? የወረት ፍቅር መሆን አለበት። "የጋራ ጠላት" የሚሉት የስድሳ ዓመት ተረት ተረት አስተሳስሯቸው ነው። ኢሕአፓ፤ መኢሶን፤ ኦነግ፤ ህወሓት፤ ሻብያ። ጠላት ፈጥረው ሲተባበሩ፤ ደግሞ ሲገዳደሉ፣ እንደ በረሓ ጂኒ እረፍት አያውቃቸውም። እረፍት አይሰጡም። "የጠላቴ ጠላት ወዳጄ" ይሉና፣ መልሰው እርስ በርስ ጠላት! ህወሓት ትናንት፦ የኢሳይያስ ወታደር ክልሌን ዘረፈ፤ ሴቶችን ደፈረ፤ ዓይንህ ላፈር ብለው "ጄኖሳይድ፣ ጄኖሳይድ" ፈክረውበት ነበር። ታዲያስ? ያ ሁሉ ትግራዋይ ደም ባጭር የቀረው ለዚህ ኖሯል? 

ከዚህ የሚጠቀሙ አሜሪካኖች፤ እንግሊዞች፤ እስራኤል፤ ኤሚሬቶች። ዐቢይ ሥልጣናቸውን ላለማስነካት የሚያስፈልገውን አገራዊ ጥቅም ይሠዋሉ። 130 ሚሊዮን ሕዝብ አለኝ ብለው ዝተዋል። 30 ሚሊዮኑ ቢሠዋ፣ ገና 100 ሚሊዮን ይቀረኛል አባባል። ሰብ ዓዊነት የጎደለው ጭካኔ የተመላ ስሌት ነው። የደብረጽዮንም የኢሳይያስም አካሄድ ተመሳሳይ ነው። ስለ ራሳቸው፣ ስለ ሥልጣናቸው እንጂ ስለ ሰው ደም ገድዷቸው አያውቅም!

ባለፈው ጦርነት አሜሪካኖች ህወሓትን አዲሳባ ለማግባት ወስነው ነበር። ጀግናው ዐቢይ ጦርነቱን ለመምራት ወደ ጦር ሜዳ ዘምተው፣ ብዙ ሳይቆይ፣ ድል አደረግን ብለው አወጁ። ድል ሳናደርግ ነው ታዲያ። ከሁሉ የሚገርመው የህወሓት አፈ ቀላጤ የዛሬው የዐቢይ አማካሪ ጌታቸው ረዳ ነበር። 

አንድ ጌታቸው ረዳ፣ ብቻውን የዐቢይን መንግሥት በወሬ ብቻ በዓለም ፊት ሲያሳጣ ሲያርበደብድ ነበር። ዐቢይ ወይ ራሳቸው ወይ ሌላ ሰው ወይም ድርጅት የኢትዮጵያን ጉዳይ እንዲያስረዳ ማድረግ አልቻሉም፤ አላወቁበትም! እስከ ዛሬ ከስሕተታቸው አልተማሩም። 

ሰባቱ "አካታቾች" "ጽምዶ" ተሰኝተዋል። "ጽምዶ!" አጠራሩ ማ አለቃ ማ ጀሌ እንደ ሆነ ያሳብቃል። ኦሮሞው አማራው ከኤርትራና ትግራይ የሚተካከል ልምድና ትጥቅ የለው። የኤርትራና ትግራይ አዛዦች አድርባዩን በምሥጢር መልምለው በጦሩ ውስጥ ሠግሥገውለታል። ምልምሎቹ አማራ ናቸው፤ ኦሮሞ ናቸው። ወይም ኦሮምኛ ይናገራሉ፤ አማርኛ ይናገራሉ። ኃይማኖታቸው ሥልጣን፣ ሆድና ንዋይ ነው! አሳልፎ ለመስጠት የሚቆረቊራቸው ኅሊና የላቸውም! ምን ማ ትዝ አለን?

ጦር መሳሪያ የሚያቀብለው ኢሳይያስ ከግብፅ ተቀብሎ ነው። በስተ ፍፃሜ፣  ሥልጣንም ሳይይዝ፣ ለስም ብቻ አማራን ኦሮሞን ወክል ብለውት ትርፍራፊ ይጥሉለታል። ሥልጣን ላይ ሲወጣ፣ ለታገልኩበት ለደማሁበት ካሳ የሚሆነኝን ያህል ካልዘረፍኩ ይላል። የገዛ ወገንህን (አማራውን ኦሮሞውን) ዝረፍ ይሉታል። ትግራዩ ኤርትራው ጋ እንኳ እንዳትደርስ። ለነገሩ የሚዘረፍም የለም፤ ይልቊን ደግሞ ጂኦግራፊ አይፈቅድልህም ይሉታል። ወደ ዝርፊያ ሲከንፍ አለቆቹ እንደ ለመዱት የራሳቸውን ሳያስነኩ እያተራመሱ ንብረት ያግዛሉ። ግርግር ለሌባ ያመቻል። ምን ማ ትዝ ይለናል?

አገራችን ከዚህ እርግማን እንዴት መላቀቅ ትችል ይሆን? ሰሞኑን አንሠራርተው ከመጡት "አካታቾች" አንዳንዶቹ፣ ዐቢይ እግዚአብሔር ተናገረኝ ብለው ከእስር የፈቷቸው የህወሓት አለቆች ናቸው። መፍታት ብቻ ሳይሆን ንብረታቸውን ሁሉ መልሰውላቸዋል! ግራ የተጋባነው መሪዎቻችን ግራ ስለ ገባቸው አይደለ?  ግራ የተጋባነው መሪዎቻችን፣ ዜጋ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንዳይኖረው፣ ምንም ዓይነት ጥያቄ እንዳያነሳ ስለ ከለከሉት አይደለ? ሕዝብ በልቡ ከድቷቸው፣ ብቻቸውን እንደ ቀሩ አልተገነዘቡም። የሚያሳዝነው፣ ነገር ከባሰ ሁላቸውም አገር ጥለው የሚፈረጥጡ ናቸው። ገፍቶ ከመጣ፣ ዐቢይ ወይ ዓይን ያወጣ አገር የሚያዋርድ ድርድር ያደርጋሉ። ወይም ወደ ወዳጆቻቸው ወደ ፋሺስት ወ/ሮ ሜሎኒ እና ወደ ጠቅላይ ፕሬዚደንት ቤን ዛይድ ይሸሻሉ። 

እግዜር ያቅልልልን። 

Popular posts from this blog

HaileSelassie's Band of Armenian Orphans

The Prince and the Maharaja

Home of the Shy