በአዲሱ ዓመት እውነት የሚናገሩ እግዚአብሔር የሚፈሩ ሕዝብ የሚያከብሩ መሪዎች ያስነሳልን
ለ2019 ዓም ዘመን መለወጫ ከጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የተላለፈ መልእክት። የሚንስትሩን ቃል አንባቢ ከሕዝቡ ኑሮ ጋር እያስተያየ በጥንቃቄ ያንብብ። በያመቱ ይህን የመሰሉ የምኞት መግለጫዎችን ሰምተናል። ጥያቄው፦ ዐቢይ ሥልጣን ከያዙበት ከ2010 ዓም ጀምሮ የሕዝቡ ኑሮ ምን ያህል ተሻሻለ የሚለው ነው። እርግጥ ነው፣ አገር ማስተዳደር ቀላል አይደለም፤ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያለች አገር። ዋነኛው ችግር አለመተማመን ነው። ዐቢይን ሕዝብ ያምናቸዋል? ዐቢይ ሕዝብ እንዳያምናቸው ድርሻቸው ምን ያህሉ ነው? አጻጻፋቸው ሁልጊዜ በ"እኛ እና በ"እነርሱ" ከፋፍሎ ነው፦ እነዚያ "ሕዝብ የከፋፈሉና የጨረሱ ..." ተብለዋል። (እኛ ግን) "አስደናቂ ታሪኮችን እየሰራን ነው።" "ፈጣሪ" ከእኛ ጋር ነው... ከእነዚያ ጋር ግን አይደለም!
እውነቱ ይህ ነው፦ ብዙሓኑ ሕዝብ ይኸ ዓይነት ንግግር የተጋነነ እንደ ሆነ አውቆ እጅ እጅ ብሎታል። ከመሰልቸቱ ብዛት ልቡን ሰጥቶ አያደምጠውም። ይኸ የሕዝብ አኳኋን ለአገር መሪ ትልቅ አደጋ ቋጥሯል። አፄ ኃይለሥላሴን መንግሥቱ ኃይለማርያምን መለስ ዜናዊ አገር የከዳቸው ድንገት ባንድ ጀምበር አይደለም። ቀድሞውንም ከድቷቸው ኖሮ ጊዜ ሲፈቅድለት የሸሸገውን ልቡን ገልጦ ነው። እግዚአብሔር እግዚአብሔር የሚሉት ዐቢይ፣ ልባቸውን እንዲመክርላቸው ቢፈቅዱለት ለርሳቸውም ለአገርም በበጀ። ሌላኛው ችግር፣ ዐቢይ መስማት የማይፈልጉት እውነታ በአደባባይ እንዳይነገር ማገዳቸው ዋጋ ማስከፈሉ ነው። የተከበቡት ከታሪክ እውነት በራቀ ምኞትና፣ ሊሰሙት በሚሹት ቃላት በሚክቧቸው አድርባዮች ነው። ከላይ የጠቀስዃቸው ሦስት መሪዎችን ከሕዝብ ያራቃቸው ለውርደትና ለውድቀት የዳረጋቸው እንዲህ ዓይነቱ የሕዝብ ስሜት አፋኝ አመራር ነው። ለአገራችን ለሕዝባችን ሰላም ይሁን። "ሀገራዊ ምክክር" ቢሳካ የሚጠላ የለም። እንደ ተወራው ባይሳካ ትልቁ እንቅፋት ዐቢይ ናቸው፦ ተሳስቻለሁ እታረማለሁ የማይሉት፣ የሌሎች አሳብ ከርሳቸው አሳብ ጋር ካልተስማማ ስንዝር የማይሰጡ ዐቢይ።
እውነቱ ይህ ነው፦ ብዙሓኑ ሕዝብ ይኸ ዓይነት ንግግር የተጋነነ እንደ ሆነ አውቆ እጅ እጅ ብሎታል። ከመሰልቸቱ ብዛት ልቡን ሰጥቶ አያደምጠውም። ይኸ የሕዝብ አኳኋን ለአገር መሪ ትልቅ አደጋ ቋጥሯል። አፄ ኃይለሥላሴን መንግሥቱ ኃይለማርያምን መለስ ዜናዊ አገር የከዳቸው ድንገት ባንድ ጀምበር አይደለም። ቀድሞውንም ከድቷቸው ኖሮ ጊዜ ሲፈቅድለት የሸሸገውን ልቡን ገልጦ ነው። እግዚአብሔር እግዚአብሔር የሚሉት ዐቢይ፣ ልባቸውን እንዲመክርላቸው ቢፈቅዱለት ለርሳቸውም ለአገርም በበጀ። ሌላኛው ችግር፣ ዐቢይ መስማት የማይፈልጉት እውነታ በአደባባይ እንዳይነገር ማገዳቸው ዋጋ ማስከፈሉ ነው። የተከበቡት ከታሪክ እውነት በራቀ ምኞትና፣ ሊሰሙት በሚሹት ቃላት በሚክቧቸው አድርባዮች ነው። ከላይ የጠቀስዃቸው ሦስት መሪዎችን ከሕዝብ ያራቃቸው ለውርደትና ለውድቀት የዳረጋቸው እንዲህ ዓይነቱ የሕዝብ ስሜት አፋኝ አመራር ነው። ለአገራችን ለሕዝባችን ሰላም ይሁን። "ሀገራዊ ምክክር" ቢሳካ የሚጠላ የለም። እንደ ተወራው ባይሳካ ትልቁ እንቅፋት ዐቢይ ናቸው፦ ተሳስቻለሁ እታረማለሁ የማይሉት፣ የሌሎች አሳብ ከርሳቸው አሳብ ጋር ካልተስማማ ስንዝር የማይሰጡ ዐቢይ።
ጦርነት አውዳሚ ነው፤ በነፍጥ የሞከርነው ከድጥ ወደ ማጥ እንጂ እንዳሰብነው ተሳክቶልን አያውቅም። ሸኔ ፋኖ እና ወያኔ ነፃ እናወጣሃለን ላሉት ሕዝብ ድርብ ሥቃይ ናቸው፦ ፌዴራል መንግሥት ካመጣበት መጉላላት በተጨማሪ እያስፈራሩት ደም እያቃቡት የባሰ እያደኸዩት ነው። ይኸን የሚያደርጉት ሥልጣን ላይ ለመቆያ ነው። በሕዝብ ደም የሚነግዱ ናቸው። እነ መለስ ዜናዊ በጎሳና በቋንቋ ከፋፈሉን። ዐቢይ፦ ያለእኔ፣ ያለብልጽግና ከቶ አይታሰብም ብለዋል (በአደባባይ፣ ደጋግመው)። ዐቢይ ኢትዮጵያውያንን ከፋፍለዋል (ክልል በክልል መደመር መደመር እያሉ)፦ በወጣትና ሥር በሌለው የወደቀ ዛፍ ባሉት ትውልድ። አገር ቤት ባለውና በስደት በሚኖረው። ብቃትና ልምድ ያለው ዜጋ በርቀት ታግዶ ለአገር ሳይሆን ለዐብይ ታማኝ የሆነው ለአገር የማይበጀ ተሸልሞ እያየን ነው። በባለጸጋና በተቀረው ሕዝብ መካከል (ባለጸጋ ይመረጣል፤ አገር ቢዘርፍ ምንም አይደረግም፤ ብዙሓኑ ሥራ እንዳይሠራ የሥራ እድል የለም፤ በእርሳቸው ምጽዋት እና በአምላኩ ተስፋ እንዲያደርግ ይነገረዋል፤ መርሮት ቢሰደድ አገር አሰዳቢ ይባላል፣ ወዘተ)። ምሕረት ለአገራችን ከጌታ ፀባዖት። እውነት የሚናገሩ መሪዎችን አይንሳን!
እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ፣ አደረሰን!!
ዘመን ከፈጣሪ ለሰው የተሰጠ የመሥሪያ መጽሐፍ ነው። ይህ የመሥሪያ መጽሐፍ ለእያንዳንዱ ሰው የተሰጡ የተወሰኑ ገጾች አሉት። የመጨረሻው ገጽ ተጠናቅቆ የማጠቃለያው ሽፋን እስኪከደን ድረስ የፈለግነውን የመጻፍ መብት በእጃችን ነው። አንዳንዶች ዓለምን የቀየሩ ሐሳቦችንና ሥራዎችን፤ ሌሎች ታሪክን የቀየሩ ዕሳቤዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ጽፈውበታል። በተቃራኒው ዓለምን ያወደሙ፤ ሕዝብ የከፋፈሉና የጨረሱ፤ ተፈጥሮን ያዛቡ፤ ክፋትንና ጭካኔን ያስተማሩ ሐሳቦችንና ተግባራትን የጻፉበትም ጥቂት አይደሉም። ስንፍናንና ድንዛዜን፣ ዕንቅልፍንና ሐኬትን የጻፉም አሉ።
ኢትዮጵያውያን በዚህ የዘመን መጽሐፍ ውስጥ ምን እየጻፍን ነበር? አሁንስ ምን እየጻፍን ነው? ወደፊትስ ምን ለመጻፍ እናስባለን? ከኋላችን ያሰናበትነው አሮጌ ዓመት እና ከፊታችን የምንቀበለው አዲስ ዓመት እነዚህን ጥያቄዎች እንድንመልስ ያስገድዱናል። ዓለምን ያስደነቁ የንግድ፣ የግብርና፣ የሥነ ሕንጻ፣ የዘመን አቆጣጠር፣ የሥነ ከዋክብት፣ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር፣ ሥነ ሥዕልና ሥነ ዜማ፣ ሃይማኖትና ፍልስፍና - በዘመን መጽሐፋችን ውስጥ የጻፍንባቸው የዘመን ገጾች አሉን።
በተቃራኒው ረሃብና ቸነፈር፣ ጦርነትና እልቂት፣ መከፋፈልና መለያየት፣ ማነስና መድከም፣ የጻፍንባቸው የዘመን ገጾችም አሉን።
የትናንቱ ዘመን ጠባሳውንም ዐሻራውንም፣ ዕዳውን ምንዳውንም ሰጥቶን አልፏል። አሁን ወሳኙ ነገር በቀሩን ዘመናት ምን ቁም ነገር እንሰራለን? የሚለው ነው።
ኢትዮጵያውያን ዛሬ ለትውልድ የሚተርፍ አስደናቂ ታሪኮችን እየሰራን ነው። አረንጓዴ ኢኮኖሚን በአረንጓዴ ዐሻራ፤ ቱሪዝምን በገበታ ፕሮጀክቶች፤ የምግብ ሉዓላዊነትን በበጋ ስንዴና በሌማት ትሩፋት፤ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በኢትዮጵያ ታምርት እየገነባንና እያጸናን ነው። የኢነርጂ ዐቅማችንን በተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክትና ኑክሌር ቴክኖሎጂ ለማሳደግ፤ የአፈር ማዳበሪያ ግብአቶችን በሀገር ውስጥ ለመሸፈን፤ የአየር መንገድ አድማሳችንን በግዙፉ የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ ፕሮጀክት ለማስፋት፣ ነገን አስበን ዛሬ እየተጋን ነው።
የሕዳሴ ግድብን ፍጻሜ፤ የመስኖ ግድቦችን ፍሬ፤ የሩዝ ምርትን ከፍታ፤ የፍራፍሬ ምርትን ተአምር፤ የወጪ ንግድን ጭማሬ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያችንን ውጤት፤ በአፍሪካ የፈጠርነውን የኢነርጂ ትሥሥር፤ ዲጂታል 2030ን ስኬት፤ የኮሪደር ልማታችን የኢትዮጵያን ሀብትና ውበት መግለጥ፤ የዘመን መጽሐፋችን እየመዘገበ ነው። የወንዝ ዳርቻ ልማታችን አፈራችንንም፣ ከተማችንንም፣ ጤናችንንም፣ ውኃችንንም እየጠበቀ መሆኑን፤ መድኃኒት የማምረት ደረጃና ዐቅማችም እያደገ መሄዱን፤ የማዕድን ፍለጋችን፣ ምርታችንና ሽያጫችን የዘመናት ስብራትን እየጠገነ መምጣቱን፤ የባሕር በር አጀንዳችን ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ማግኘቱን፤ የኢትዮጵያ የተጽዕኖ አድማስ መስፋቱን - የዚህ ዘመን የመጽሐፉ ገጾች እያሠፈሩ ናቸው።
እነሆ የዘመን መጽሐፋችንን የ2019 አዲስ ምእራፍ የምንጀምረው ሀገራዊ ምክራችንን በስኬት አጠናቅቀን ነው። ይሄንን ምክክር ለዘመናት ኢትዮጵያውያን ይጠይቁት ነበር። ችግራችንን በጦርነት ከመፍታት ይልቅ ለምን አንመካከርም ይሉ ነበር። በየብሔረሰቡ ያለውን የመነጋገርና የመመካከር ባህል ለምን ወደ ፖለቲካው አናመጣውም ይሉ ነበር። የዘመን መጽሐፍ ገጾችን ስናነባቸው ይሄን ጥያቄ ያቀረቡ ወገኖች ብዙ ዋጋ መክፈላቸውን ያስነብቡናል። እኛ ግን ሐሳቡን አመንንበት፤ አምነንም ተቀበልነው፤ ተቀብለንም ተገበርነው። ማመናችንና መተግበራችን ትክክል እንደሆነ የሚያሳዩ ውጤቶችንም ምክክሩ አስገኘልን።
የመጀመሪያው ውጤት “የጠላት ሟርት መክሸፉ” ነው። ኢትዮጵያውያን ሊመካከሩ አይችሉም፤ ቢመካከሩን ወደ ተቀራቢ ሐሳብ አይደርሱም የሚለውን ሟርት አክሽፈነዋል። ለመመካከር እንደምናቅድ፤ አቅደን እንደምንጀምር፤ ጀምረን እንደምንጨርስ በሀገራዊ ምክክር አስመስክረናል። ብዝሃ ሐሳቦቻችን በሀገር ጉዳይ የጋራ አቋም ከመያዝ እንደማያግዱን በተግባር አይተናል።
ሁለተኛው “ባህሉ” ነው። ከፀሐይ በታች ባሉ ጉዳዮች የመወያየት፣ የመነጋገርና የመግባባት ፖቲካዊ ባህልን ማዳበራችን ታላቅ ስኬት ነው። ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የልሂቃን ጉባኤ አድርጋ ይሆናል። ለሕዝቡ “እኛ እናውቅልሃለን” የሚሉ ልሂቃን፥ የሀገርን ችግሮች በመፍታት ስም የሥልጣን ክፍፍል የሚያደርጉባቸው ጉባኤዎች ተካሂደዋል። የዘመናት ጥያቄዎቻችን ግን መፍትሄ አላገኙም። ከልሂቃን ድርድር ይልቅ ሕዝባችን ራሱ መክሮ ራሱ መፍትሔ የሚያመለክትበት ሀገራዊ ምክክር ማድረግ ያስፈለገን በዚህ ምክንያት ነው። በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ በደማቅ ብዕር የሚጻፍ ታላቅ ጉባኤም ተናወነ።
በተካሄደው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሕዝባችንን ዋና ባለቤትና ዋና ተዋናይ በማድረግ ተጠናቅቋል። ሁሉንም አካባቢዎች፤ ሁሉንም ብሔረሰቦች፤ ሁሉንም እምነቶች፤ አብዛኞቹን የፖለቲካ አመለካከቶች፤ ሀገር ቤቱንና ዳያስፖራውን፤ ገበሬውን፣ አርብቶ አደሩንና ወዛደሩን፤ የሥራ ኃላፊዎችንና መደበኛ ዜጎችን፤ የተማሩትንና ያልተማሩትን፤ ወንዶችንና ሴቶችን፤ በዚህ መጠን በአንድ ጉባኤ በአንድ ቦታ ማገናኘት አዲስ ታሪካችን ነው። በዘመን መጽሐፍም በወርቅ ቀለም ተጽፏል።
ሦስተኛው “ውጤቱ” ነው። በአጀንዳዎች ላይ ተግባብተናል። እነዚህ ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች አንድ በአንድ ወደ ተግባር የሚወሰዱ ናቸው። ባህል የሚሆኑ አሉ። ሥርዓት የሚሆኑ አሉ። አሠራር ተደርገው የሚዘረጉ አሉ። ዕሳቤ ሆነው የምንመራባቸው አሉ። ዐዋጅ ሆነው የሚወጡ አሉ። የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳቦች የሚሆኑ አሉ። የመዋቅር ማሻሻያ የሚሆኑ አሉ። የነገዎችን ትእምርቶች፣ ሐውልቶች፣ ስያሜዎችና ሀገራዊ ብራንዶች የሚወስኑ አሉ። የትናንት ጉዟችንን የሚያርሙ፣ የሚያስታርቁና በተሻለ መግባባት የሚተረጉሙ አሉ።
መንግሥት ሁሉንም ሐሳቦች በተገቢው መንገድ ይጠቀምባቸዋል። የኢትዮጵያን የነገ ጉዞ በሚያቃና መልኩ ግብአት ሆነው ያገለግላሉ። በየጊዜው የሚጠቀሱ፣ የሚወሱና የሚነሡ ዕሳቤዎች ይሆናሉ። የኢትዮጵያ የዘመን መጽሐፍ ከሀገራዊ ምክክሩ በፊትና በኋላ የተለየ ነገር እንደሚጽፍ አምናለሁ። የመግባባት፣ የመስማማትና የመሰናኘት ጉዟችን እየሠመረ መሄዱን ይመዘግባል። የተግባባንባቸው ሐሳቦች መሬት ወርደው፣ ሥር ይዘው፣ ፍሬ ማፍራታቸውን ይተርካል።
ሀገራዊ ምክክራችን ገደ መልካም መሆኑን በምክክሩ ብቻ ሳይሆን በውጤቱም እያሳየ ነው። በአዲስ ዓመት ዋዜማ በመቶ የሚቆጠሩ ታራሚዎችን መንግሥት በምሕረት እንዲፈቱ አድርጓል። ይሄንን ያደረገበት ዓላማ ሁለት ነው። የመጀመሪያው የሀገራዊ ምክክሩን ውጤት በፍቅር፣ በይቅርታና በሰላም ለመጀመር ነው። ወደ ሀገራዊ ምክክር የመጡ ልዩ ልዩ ወገኖች በአንድም በሌላም ስሕተት የታሠሩ ወገኖች በይቅርታ እና በህግ አግባብ እንዲፈቱ ጠይቀው ነበር። መንግሥት ይሄንን ተቀብሎ በሂደቱ የተስማሙትን ፈትቷል። የምክክሩም ዓላማ ኢትዮጵያውያን በጉዳዮች ላይ እንዲነጋገሩ የተግባቡባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች እንዲያቀርቡ ነው። መንግሥትም ለምክክሩ ሐሳቦች ትግበራ ያለውን ቁርጠኝነት በዚህ የይቅርታ ሂደት ማሳየት ጀምሯል።
በዚህ የይቅርታ ሂደት የተፈቱ ወገኖች በሀገራዊ ምክክር ምክረ ሐሳቦች ላይ አዎንታዊ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይታመናል። ካለፈው መንገድ በመማር የወደፊቱን መንገድ የሰላምና የዴሞክራሲ መንገድ ያደርጉታል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል። ማኅበረሰቡም እነዚህ ወገኖች በሀገር ሰላምና ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ማገዝና መምከር አለበት።
መነጋገር፣ መከራከርና መፎካከር ሲቻል ግጭትና ጦርነት አዋጪ አይደለም። የብዕርና የሐሳብ ጊዜ እንጂ የጠመንጃ እና የጉልበት ጊዜ አልፏል። የኢትዮጵያ የዘመን መጽሐፍ ካሁን በኋላ የጠመንጃና የጉልበት ታሪክን አይመዘግብም። በታሪካችን ውስጥ በቂ ግጭቶችና ጦርነቶች መኖራቸውን የዘመን መጽሐፋችን አሳይቶናል። ቀጣዩ ምእራፍ አዳዲስ መንዶችን እንጂ አሮጌ አካሄዶችን አይመዘግብም።
ቀጣዩ ዓመት የጉባ ብሥራቶችን የበለጠ ተግባራዊ የምናደርግበት ዘመን ይሆናል። የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቶ የተለያዩ ዕሳቤዎችንና አካሄዶችን በብሔራዊ ጥቅም አስተሣሥረን የምንጓዝበት ዓመት ይሆናል። ሁለንተናዊ ሉዓላዊነታችን ይበልጥ የሚከበርበት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ይበልጥ የሚጸናበት፣ በሁሉም ዘርፎች የጀመርነው ምርታማነት በዓይነትና በጥራት የሚጨምርበት፣ ሀገራችንም የቀጣናውና የአፍሪካ መሪነቷን ሥር መሠረት የምታስይዝበት፤ የኢትዮጵያ ብልጽግና ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን ተደርጎ የሚገነባበት ዓመት ይሆናል።
ይህ እንዲሳካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ፣ የልሂቃን ሚና፣ የሃይማኖት አባቶች ጸሎት፣ የጸጥታ ተቋማት ጥንካሬና ቁርጠኝነት፣ የአምራች ኢንዱስትሪው ትጋትና ብርታት፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ቅልጥፍናና ለሕዝብ አሳቢነት፣ የገበሬውና የአርሶ አደሩ አይበገሬነት፣ የወጣቶችና ሴቶች ያላሰለሰ ጥረት፣ የሚዲያዎች ሐቀኝነት፣ የዲጂታል ዘርፉ ዘመናዊነት፣ የሲቪል ሰረቫንቱ ንጽሕናና አገልግሎት፣ እጅግ ወሳኞች ናቸው።
አዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ የዘመን መጽሐፍ ላይ አዲስ ታሪክ፣ አዲስ ሐሳብና አዲስ ሥልጣኔ የምንጽፍበት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ይህ እንደሚሆንም አምናለሁ። ፈጣሪም እንደሚረዳን እተማመናለሁ።
መልካም አዲስ ዓመት።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ጳጉሜን 5፣ 2018 ዓ.ም
Comments
Post a Comment