አንቀላውጥ፣ ያለው ይበቃናል
አንቀላውጥ፣ ያለው ይበቃናል
ክፍል
አንድ፦
እስከ
1966 ዓም
ድረስ
"የኢትዮጵያ
ሕዝብ መዝሙር” ኢትዮጵያ ሆይ! ደስ ይበልሽ! ነበር። በማን ደስ ይበልሽ? በአምላክሽ። በንጉሥሽ። አምላክሽ እና ንጉሥሽ አይነጣጠሉም፤ ሁለቱም ድል አድራጊ ናቸው። ሁለቱም አይደረስባቸውም። ንጉሥ አይከሰስም፤ ሰማይ አይታረስም።
ብቻ
ኢትዮጵያ
ደስ ይበልሽ። ድህነትሽን ጉስቊልናሽን አታስቢ። ንጉሥሽ ክብርሽ ነው፤ በድህነትሽ አትፈሪ። አምላክ አለልሽ። ንጉሥ አለልሽ። በምድር ያጣሽውን በሰማይ ትካሺያለሽ።
[ግጥም፦ ዮፍታሔ ንጉሤ። ዜማ (አርመናዊው) ነርሲስ ናልባንዲያን]
ክፍል
ሁለት፦
ደርግ
መጥቶ፦ የምን ንጉሥ ነው? ወዲያልኝ አለ። የምን እግዚአብሔር? ወዲያልኝ አለ። ከ1967ዓም እስከ 1984ዓም የኢትዮጵያ ልጆች ባንድነት፦ "ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቅደሚ" አልን።
[ግጥም፦ አሰፋ ገብረ ማርያም ተሰማ። ዜማ፦ ዳንኤል ዮሐንስ ሐጎስ]
ክፍል
ሦስት፦
እነ
መለስ በ 1983 ዓም ብቅ አሉ፤ ተራቸውን፦ የምን ደርግ ነው? አገርን በመደብ የከፋፈለ ደርግ ፋሲሽት ነው አሉን። ደርግ ጦርነት እንጂ ሰላም አያውቅም አሉን። እንደ ደርግ እነርሱም እግዚአብሔርን ረሱ። እግዚአብሔርን፣ ኅብረሰባዊነትን (ኅብርን) በ “ህዝቦች” ለወጡ። የጦርነቱን አናንሳ። የኢትዮጵያን ህዝብ በ ህዝቦች ተኩ።
[ግጥም፦ ደረጀ መላኩ መንገሻ። ዜማ፦ ሰሎሞን ሉሉ ምትኩ]
ክፍል
አራት፦
ሰሞኑን፣
ብልጽግና
(ወይም በሌላ መጠሪያው፣ የምክክር ኮሚሽን፤ ወይም በትክክለኛ መጠሪያው፣ ዐቢይ አሕመድ) ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር እየተነጋገረ መሆኑን እየሰማን ነው። ጠ/ሚ ዐቢይ 7ኛው ንጉሥ ነኝ ከማለታቸው ጋር፣ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የተዘመረው መዝሙር ስለሚስማማ፦ በንጉሥሽ ይላልና። ዐቢይ፣ የብልጽግና ወንጌል አማኝ ነኝ፤ የሰው መካሪ ሳያሻኝ፣ የማማክረው ቀጥታ እግዚአብሔርን ነው ብለዋልና (በአደባባይ ከተናገሩት)፣ በአምላክሽ ኃይል ይላልና። ወደ ቀድሞው ልንመለስ ይሆን?
በሌላ
አነጋገር፣
እነ መለስ በ1983ዓም አዲሳባ ከገቡበት እለት ጀምሮ ሁለት ትውልድ እንኳ ሳይሞላ በአንድ ትውልድ ተኲል (በ 35 ዓመት)፣ ሦስት ብሔራዊ መዝሙር ልንዘምር ይሆን? የየክልሉ ዝማሬ ወደ ብሔራዊው ሊደመር ይሆን? እንጃላቸው። ዜጋ ተርታ ሕዝብ እንደ ሆነ አይጠየቅ! ምን ያውቃልና ነው? ምን አገባውና ነው? የሕዝብ ተወካይ የተባለው ራሱን በራሱ የሾመ ነው!
እንደ
እውነቱ ከሆነ፣ በየዘመኑ የተዜሙት ብሔራዊ መዝሙሮች ብዙም ልዩነት የላቸውም። “ኢትዮጵያ ደስ ይበልሽ” “ኢትዮጵያ ቅደሚ” “ወደፊት ገስግሺ”። ሁላቸውም ለአገር በጎ እንዳሰቡ ግልጽ ነው። ጥያቄው፦ ይህንን በጎ ምኞታቸውን ምን ያህሉን ተግባራዊ አድርገውታል ነው። ሕዝቡን ምን ያህል አክብረው ራሱን እንዲያስተዳድር ህጉን ቀርጸዋል ነው? መሪዎቹ ራሳቸው ምን ያህል ለህግ ተገዥ ሆነዋል ነው። እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ትቶ ሌላ አዲስ ብሔራዊ መዝሙር ማውጣት አስፈላጊ አይመስለኝም። ማታለል ነው። ጊዜና ገንዘብ ማባከን ነው። ሕዝብን ወይም አገርን ሳይሆን ራስን ማግነን ነው። ችግሩ ያለው መሪዎች ጋ እንጂ የሕዝቡስ ጉዳይ ዳቦ ልብስ ህክምና ሥራ መኖሪያ ቤት በሰላም ወጥቶ መግባት መከበር መከባበር። በወሬ መደንቆር ሳይሆን በሚጨበጥ ተስፋ ቃላቸውን በማይለዋውጡ በታመኑ መሪዎች መመራት ነው!
ሥጋቴ
ይህ ነው፦ አዲስ ብሔራዊ መዝሙር፣ የጠ/ሚ ዐቢይን ብልጽግና ወይም መደመር ያሉትን፣ ኢትዮጵያም እንደ እስራኤል በእግዚአብሔር የተመረጠች የክርስቲያን አገር ነች፤ በብልጽግና ወንጌል እና በዐቢይ አመራር ወደ ቀድሞ ከፍታዋ ትመለሳለች የሚለውን ዝባዝንኬ ለማደርጀት እንዳይሆን ነው።
አገራችን ኢትዮጵያ ክርስቲያኖች የሚኖሩባት አገር ነች፤ ክርስቲያን አገር ግን አይደለችም። አገራችን ኢትዮጵያ እስላሞች እና ሌላ እምነት ያላቸው የሚኖሩባት አገር ነች፤ እስላም ወይም የሌላ እምነት ተከታይ አገር አይደለችም። ባጭሩ፣ ኢትዮጵያ ክርስቲያን መንግሥት አያስፈልጋትም። የሚያስፈልጋት፦ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ብቃት እና ልምድ ያላቸውን ነው!
ኢትዮጵያ
ሆይ! ወደ ኋላ ወደ ኋላ እያልሽ አትዘግዪ፤ ባልተረጋገጠ፣ ባረጀ ህልም በቅዠት ዛሬና ነገን አትሞክሪ። ካለፈው የሚረባሽን ወስደሽ ወደ ፊት ገስግሺ ካልን በቂ ይመስለኛል፦
በሙሉ ልብ ካዜምን፣ ከተከባበርን፣ ፍትኅ ካሰፈንን፣ የአገራችንን ህልውና ከጠበቅን፣ በአገር እና በሕዝብ መኩራት ከቻልን። አዲስ መዝሙር አያሻንም፤ ያለን ይበቃናል።
Comments
Post a Comment