ነጠላ አጀንዳ ለቤተ ክርስቲያን ምስክርነት እንቅፋት ነው

 ነጠላ አጀንዳ ለቤተ ክርስቲያን ምስክርነት እንቅፋት ነው

ትልቁ ጥያቄ፦ የኢትዮጵያ ወንጌላዉያን አብያተ ክርስቲያናት ከሚሲዮናዊ ድርጅቶች የገንዘብ እና የማቴሪያል እርዳታ ነፃ የምንወጣው መቸ ነው? የሚለው ነው። ገንዘብ ወይም "ሥልጠና" ለመቀበል የማንጓዘው መንገድ የለም! የአሜሪካ ወንጌላዉያንን አካሄድ እንዳ መኮረጅ አቁመን በራሳችን መወሰን የምንጀምረው መቸ ነው? እነርሱ እድሜ ልክ ተጧሪዎች ተረጂዎች እና ጨቅላዎች ብንሆን ቅር የሚላቸው አይመስልም። በኢትዮጵያ ሕፃናት፣ ሴቶችና ተረጂዎች ስም ገንዘብ ማሰባሰብን አትራፊ ንግድ ያደረጉትን፣ በስማችን እንዳይነግዱ የምናግደው እንዴትና መቸ ነው? 10 ሺህ ሰው አመነ ተጠመቀ ወይም በሦስት ዓመት 50ሺህ ፓስተሮች ሥልጠና ተሰጥቷቸው በዲፕሎማ ተመረቁ (ፎቶ) (እየቀለድኩ አይደለም) 10ሺህ ቤተ ክርስቲያኖች ተተከሉ (ፎቶ) የሌለ። ማመን ጨርሶ የሚቸግር! በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ድርጅቶች በዚህ ተግባር ተሠማርተዋል። በአፍሪካ አገራት ካንዱ ወዳንዱ እየዘለሉ። እርግጥ አንዳንድ ቅኖች አይታጡም። ባብዛኛው ግን ራሳቸውን የሚያበለጽጉ ናቸው። ለቤተ ሰቦቻቸው በሕልም ካልሆነ የማይገኝ የገቢ ምንጭ ሥራ ፈጥረዋል። ማርስ ሂል የተሰኘ 10 ዓመት በፊት በህንድ እና በኢትዮጵያ ስም 10ሚሊዮን ዶላር አርዳታ አሰባስቦ 10 ፐርሰንት ያህል ብቻ ለሁለቱ አገራት አውሏል። የተቀረው እዚሁ አሜሪካ ቀርቷል!

ፍራንክሊን ግራሃም፣ ልጁን ኤድ ግራሃምን አስከትሎ መስቀል አደባባይ ላይ ሕዝብ ሲያሰባስቡ እኛ የሌለ ምን አምጥተው ነው? (ይህን በመሰለ ሁኔታም ውስጥ እግዚአብሔር አልሠራም ለማለት አይደለም!) ጊዜ ካገኛችሁ፣ የተካሄደውን ስብሰባ፣ አሜሪካ ከተሠራጨው ሪፖርት ጋር አስተያዩ። አባቴ ቢሊ ግራሃም በኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት አዲሳባ ኢትዮጵያ እንዳደረገው አደረግኩ ነው? / ዐቢይ፣ እንደ አፄ ኃይለሥላሴ በርሊን ላይ ተገኝተው ለአውሮጳ ወንጌል ሥርጭት ኮንግረስ ንግግር አሰምተዋል (ዐቢይ "ንጉሥ ነኝ" ያሉን ናቸው) ችግሩ፣ ፍራንክሊን ግራሃም እንደ አባቱ ቢሊ ግራሃም ስለ ክርስቶስ ወንጌል ንጽሕና ብዙ አይገደውም! በአደባባይ በሚናገራቸው ወንጌልን መፃረሩ ግራ ባጋባ ቁጥር፣ የሚሰበስበው ገንዘብ እየበዛለት ከቢሊዮን ዶላር በላይ አልፏል! እውነት ለመናገር፣ በዓለም ዙሪያ ለተጎዱ እርዳታ በማድረስ፣ በዓለማውያን ድርጅቶች እንኳ የተመሠከረለት ሥራ እየሠራ ነው። ይህን መካድ አይቻልም።

ብዙዎች ወገኖቻችንም ሥራና ገቢ ስለሚያስገኝላቸው ብቻ ከውጭ ድርጅቶች ጋር ይተባበራሉ። አንዳንዶችም በእነርሱ ስልት ተሠማርተዋል። የተጋነነ፣ አንዳንዴም የሌለ ሪፖርት ያቀርባሉ። "ካውንስል ነኝ" ያለን ቤተ መንግሥት ውስጥ መመሸግ አቁሞ፣ ይህን ዋነኛ ሥራ ቢሠራ ለአገራችን አብያተ ክርስቲያናት ትልቅ ውለታ በዋለ! ሴሚነሪዎች በአገራችን ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን "ሚሲዮናዊ" ድርጅቶች ስም ዝርዝር፣ የሚንቀሳቀሱበትን አካባቢ፣ ዓላማቸውን፣ ምግባራቸውን፣ በተለይ በአሜሪካ ለሚገኙ ደጋፊዎቻቸውና ለመንግሥት የሚያቀርቡትን ዓመታዊ ሪፖርት ይኖራቸው ይሆን? ይህን አድካሚ ሥራ ለመሥራት ይፈቅዳሉ? ውጤቱንስ አብያተ ክርስቲያናት ይጠቀሙበታል? ከምእራባውያን ጋር በመቶ ዓመት ግንኙነቶቻችን ከጥገኝነት ያልወጣነው ለምን ይመስለናል?

ይህን ስል፣ ሚሲዮናውያን ወንጌልን አላመጡልንም ወይም በድካማቸው አልተጠቀምንም ለማለት አይደለም። ተባብረን የምንሠራው ሥራ አይኖርም ማለትም አይደለም፤ በመከባበር አብረን መሥራትማ አለብን። በእነርሱ የጎደለውን እኛ ልንሞላ፤ በእኛ የጎደለውን እነርሱ በጸጋቸው ሊሞሉ በክርስቶስ አንድ ቤተሰብ ሆነናል! ይኸ ትውልድ ትልቅ ሥራ ይጠብቀዋል። ደቀ መዝሙርነት የሚባል። የግለ ሰቦች ሳይሆን፣ የሃበሻ ፈረንጆች ሳይሆን፣ የዘር ክርስትና ሳይሆን፣ የኢየሱስ ደቀ መዝሙርነት! በቅድሚያ ግን ከቤተ መንግሥት ጥላ ሥር ወጥተን በክርስቶስ መስቀል ጥላ ሥር እንጠለል! የሕዝቡ ባለቤት፣ የቤተ ክርስቲያኑ አዳኝ ጌታና እረኛ አይተኛም። አያንቀላፋም። ሥራውን አያቆምም። ጽድቅ እንደ ማለዳ ጮራ እስኪወጣ ዝም አይልም። መሠረተ ክርስቶስ የወሰደችው እርምጃ መልካም ጅማሬ ነው።

ባለፈው ልጥፌ እንዳስገነዘብኩት፣ ቤተ ክርስቲያን ነጠላ አጀንዳ አንግባ ስትነሳ (ግብረ ሰዶምን) በአስተምህሮዋ ላይ ትልቅ መፋለስን ያስከትላል። ከግብረ ሰዶም ሌላ ሌሎች ዋነኛ አጀንዳዎች እንደሌሉ ማስመሰል ምስክርነታችንን ያጎድፋል። እንዳንታመን ያደርገናል። ግብረ ሰዶምን መቃወም (ተቃውሞ አያስከትልም) ሥራ አጥነትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ የፍትኅ መጥፋትን፣ የሕዝብ ንብረት ዘረፋን ግን (ችግር ስለሚያስከትል) ችላ ብንል ግብዞች ያደርገናል። ከግብዝ አፍ ወንጌልን የሚቀበል የለም! ለወንጌል ንጽሕና ለክርስቶስ ስም ስንል፣ በሁሉም ሁኔታ በሁሉም ወቅት እውነትን መናገር ግዴታና ጥሪአችን ነው። እውነትን መናገር በፍቅር መሆን አለበት፤ ግብረ ሰዶማውያንን በእግዚአብሔር አምሳል እንደ ተፈጠሩ አለመርሳት ለርኅራኄና የፈረሰን የሳተን ለማደስና ለመ መለስ በር ከፋች ነው። ከገዥው መንግሥት ጉያ መገኘታችን ምስክርነታችንን አጉድፎታል። ይኸ ባስቸኳይ መታረም አለበት!

Comments

Popular posts from this blog

HaileSelassie's Band of Armenian Orphans

The Prince and the last Maharaja

Home of the Shy, Land of the Brave