ሐዋርያ የሚለውን ስም አንሱልኝ ስለ ጌታ
"ሐዋርያ የሚለውን ስም አንሱልኝ ስለ ጌታ" ~ ሐዋርያ ዳንኤል መኰንን
[ሰይጣን] ቤተ ክርስቲያን ዐይኗን በክርስቶስ ላይ እንዳታደርግ ይከለክላል... ዛሬ የተጀመረ አይደለም፤ በራእይ ምእራፍ 2 ቊጥር 12 ላይ በጴርጋሞን ቤተ ክርስቲያን የበለዓምን ትምህርት የሚከተሉ ሰዎች ስላሉ በመካከልህ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ ቸል ብለሃቸዋል፤ ሌላ ትምህርት ገብቶ፣ ሰው ጌታን እንደማየት ተወናብዷል። ከመስመር ወጥቷል።
የትያጥሮን ቤተ ክርስቲያንማ በዚሁ በምእራፍ 2 ቊጥር 18 ጀምሮ የሚናገረው፣ ያቺ ሴት ይላታል፣ ጀዘቤል፣ ነቢይ ነኝ የምትለው፣ ይኸው፣ ነቢይ ናት አይላትም፤ ነቢይ ነኝ የምትለው፤ እኔ ነቢይ አድርጌ አልቀባኋትም ነው የሚለው ጌታ። ልጆቼ ለጣዖት የተሠዋውን እንዲበሉ፣ ችግር የለውም የምትላቸው፣ መንፈሳዊ ምንዝርና ውስጥ የምትከታቸው፤ ያቺን ሴት ቸል ስለምትላት፣ አዝኜብሃለሁ።
የእግዚአብሔር ባርያዎች፣ ለአንድ ደቂቃ ከጌታ የተሠጣችሁን ሥልጣን፣ አሳልፋችሁ ለማንም ሰው አትገዙ። ስለዚህ ብዙ ጊዜ ንስሃ እንድትገባ ሰጠኋት። ንስሃ የመግቢያው ሰዓት አሁን ነው። ሪቫይቫል በደጅ ነው (አሜን ከጉባኤ)። ሰብሮ መግባቱ አይቀርም። ገነጣጥሎ አይግባ። በክብር ግን ይግባ። (ከጉባኤ አሜን) መሥራቱ አይቀርም ጌታ። ለኢትዮፕያ የዘረጋውን አጀንዳ የሚከለክለው ሰው የለም። ኧረ የለም ማንም የሚከለክለው የለም። (ከጉባኤ አሜን) ይቺ ሴት፣ ስለዚህ ልጆቿን እገድላቸዋለሁ አለ። በአዲስ ኪዳን የተፃፈ እኮ ነው። ልጆቿን እገድላቸዋለሁ። እርሷንም ደግሞ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ፤ በበሽታ እመታታለሁ ነው። እግዚአብሔር ላላማው ጨካኝ ነው። ያንን አያሰማን። ያንን እኔ እፈራዋለሁ ወገኖች። ዛሬ ቤተ ክርስቲያን በሃሰተኞች ነቢያት እየተፈተነች ነች። ከመስመር የወጣ ነገር፣ ከቃሉ የወጣ ነገር፣ ሰምተን የማናውቀው ነገር፣ ከቀን ወደ ቀን እየተጨመረልን ነው። ነቢይ ነኝ የምትለዋ አለ።
እኔ ጄኔራል አሴምብሊ ጠራሁ። “ሐዋርያ” የሚለውን ስም አንሱልኝ ስለ ጌታ ብላችሁ። አልፈልገውም። ከንግዲህ ወዲህ "ፓስተር" ብላችሁ መጥራት ትችላላችሁ፤ መለስ ሲል "ጋሽ ዳንኤል" ማለት ትችላላችሁ። ከዚያ ያለፈ ነገር የለኝም፤ አንሱልኝ አልኩ። (ከጉባኤ የዘገየ ጭብጨባ) ግን ግልጹን ልንገራችሁ፣ "ሐዋርያ ዳንኤል" ሲሉኝ ክ-ብ-ድ ብሎኛል። ክብድ። ምን ቀን ነው እዚህ ውስጥ የገባሁት? ምን ቀን ነው? ያን ለታ ከብዶት ያየሁት ሰው (በጣት ጥቆማ) ዶ/ር ቤተ ነው። ፊቱ ላይ በደንብ አየሁበት ያን ለታ። ምነው ቀደም ብዬ ባማከርኩት? አልፈልገውም። ምክንያቱም፣ ሐዋርያት ሳይሆኑ፣ ሐዋርያት ነን የሚሉትን መርምረህ ሃሰተኞች ሆነው አግኝተሃቸዋል። ይህን እወድልሃለሁ።
ከንግዲህ ወዲህ ሐዋርያት ቢነሱ፣ በጌታ የተቀቡ፣ ክብሩን የለበሱ፣ ሕይወታቸው የሚመሰክር፣ (ከጉባኤ አሜን ጭብጨባ) ሕይወታቸው የሚመሰክር (ከጉባኤ አሜን) "ሬድ ካርፔት" አንጥፉልኝ የማይሉ፣ (ከጉባኤ አሜን)፤ ለምን? በጣም ጥሩ ጊዜ ላይ አይደለንም ያለነው። አልፈን ሄደናል። ስተናል። እዚህ ለናንተ ቀላል ነው (ዴንቨር አሜሪካ)። ኢትዮፕያ ውስጥ ያለው ቻሌንጅ፤ በሌላ ቤተ እምነቶች፣ መሳቂያ ሆነናል። ለውርደት ሆነናል። አትክደው ነገር ቪዲዮውን ያሳየሃል። ይኼው! እየው ይኸው እየው።
እኔ በአምስቱ "ኦፊስ" አምናለሁ (ኤፌሶን 4:11፦ አንዳንዶቹ ሐዋርያት (1)፥ ሌሎቹም ነቢያት (2)፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች (3)፥ ሌሎቹም እረኞች (4) እና አስተማሪዎች (5) እንዲሆኑ ሰጠ)። ግን አሠጣጡ ለእነማን መሆን እንደሚገባው፣ ወገኖች ሆይ፣ የሚወስን አባቶች ናቸው። ባይሠጥም ባይባልም ደግሞ፣ ሥራው ይመሰክራል። (አሜን ከጉባኤ ጭብጨባ)፤ ሥራው ይናገራል። (ከጉባኤ ጭብጨባ)። እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን!
አዎ ዛሬ እኮ ምን ላይ የደረስን መሰላችሁ? አንድ ሰው አንድ ቤተ ክርስቲያን ሄደ፤ እውነተኛ ነገር ነው የምነግራችሁ። ወጣት ፓስተር ነው፤ ብልጭልጭ ሱት ነው የለበሰው፤ ይኸው አለ ለጉባኤው፣ ከኢየሱስ ጋር መንግሥተ ሰማያት ሄጄ ፎቶግራፍ ተነሥቼ መጣሁ አለ። ጉባኤው ይዘላል ኡ እያለ በቃ። ምነው እኔም [ከኢየሱስ ጋር ፎቶ] በተነሣሁ ይላል።
አሁን እኛ የሚያስፈልጉን ነቢያት ስልክ ቊጥር የሚናገሩ አይደሉም። (ጭብጨባ ከጉባኤ) ኖ! (ከጉባኤ ጭብጨባ)። የቤቴን መጋረጃ ቀለም የሚነግረኝ አይደለም። አሁን ያሉ ነቢያቶች የእግዚአብሔርን ሰማያዊ ሃሳብ ተረድተው፣ ወደ ምድር አምጥተው የሚያሳዩን ናቸው። ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን! (ጭብጨባ ብዙ ጩኸት ከጉባኤ)። እግዚአብሔር በዚህ ቅባት ይቀባችሁ! (ጉባኤ ብድግ ብሎ ጭብጨባ)
መነጋገርያ ነጥቦች፦
1. ፓስተር ዳንኤል መኰንን (በመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን "ወንጌላዊ" የነበሩ) "እግዚአብሔር የለም" በተባለበት ዘመን፣ ኢየሱስን መከተል በሚያሳስርበት ዘመን፣ እግዚአብሔር ካስነሳቸው አገልጋዮቹ አንዱ ነበሩ። በ 2001 ዓም አካባቢ (ከ17 ዓመት በፊት) በ"ሐዋርያነት" ሲሾሙ ለሢመታቸው ድል ያለ ክብረ በዓል በተደረገበት ወቅት ብዙዎች ግራ ተጋብተው እንደነበር። በቃልም በጽሑፍም ባያደርጉት ይሻል ነበር እንዳሉ እናስታውሳለን።
2. ፓስተር ዳንኤል፣ "ሐዋርያ" የሚለውን ስም እንዲያነሱላቸው የጠሩት ጠቅላላ ጉባኤ ምላሹ ምን ነበር? (Gospel Light Ministries ድረ ገጽ አሁንም "ሐዋርያ" ዳንኤል ይላል።)
3. "በአምስቱ ኦፊስ አምናለሁ" (ኤፌሶን 4:11) ሲሉ፣ አባባላቸው በኤፌሶን 2:20 ላይ፦ "በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው" ከሚለው ቃል ጋር አይጋጭም? ፓስተር ዳንኤል፣ "ሐዋርያነት" በሌሎች ላይ ለመሠልጠንም እንደ ዋለ ከላይ ገልጸዋል።
4. "ሐዋርያ" እንደ ጴጥሮስ ዮሐንስ ጳውሎስ ማለት ይሆን? ከሆነ፣ "የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው" (1ኛ ቆሮንቶስ 3:10-11) ከሚለው አኳያ እንዴት ይታረማል?
5. ፓስተር ዳንኤል፦ "አሠጣጡ (ሐዋርያነት፣ ወዘተ) ለእነማን መሆን እንደሚገባው፣ ወገኖች ሆይ፣ የሚወስን አባቶች ናቸው" አባባላቸው መብራራት ይኖርበታል። "አባቶች" ከቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እና አስተዳዳሪዎች በምን ይለያሉ? እንዴትስ በማን ነው "አባት" የተሰኙት?
6. ቢዘገይም፣ ፓስተር ዳንኤል "አልፈን ሄደናል፣ እግዚአብሔርን ይቅር በለን እንበለው፣ ንስሃ እንግባ" ማለታቸው ትክክል ነው።
7. "ሐዋርያ" የሚለውን መጠሪያ አንሱልኝ እስከ ማለት የደረሱት፣ "ብልጭልጭ ሱት" የለበሰው ግለ ሰብ እና እንደ እርሱ ያሉት የሚሆኑትና የሚናገሩትን ከመፀየፍ ነው ወይስ ሌላም ምክንያት አለ?
8. የማኅበረ ሰባችን በፖለቲካውም በየቤተ እምነቱም አንዱ ባንዱ ላይ የመሠልጠን ፍላጎት፣ አለመደማመጥ አለመከባበር፣ ያስከተለው ችግር ዛሬ የምናየው አይደለም? ነባር መሪዎች (አባቶች) ለቀጣይ ትውልድ በጊዜ ሥፍራ ስላልሠጡ (ተተኪ ማፍራት) ስላልቻሉ ወጣቱ አምፆ በየፊናው አልሄደም ወይ? የምናየው የተሳሳቱ አስተምህሮዎች (ብልጽግና ወንጌል፣ የቃሉን መሠረት ያፋለሰ የግል ልምምድ፣ ዘረኝነት፣ ተከፋፍለው የከፋፈሉን ኢትዮጵያዊ/ሚሲዮናዊ 'ሚኒስትሪዎች') ውጤት አይደለም ወይ? የየአብያተ ክርስቲያናቱ መሪዎች ("አባቶች") ቀድሞ ከመቧደን አልፈው መቸ ተደማመጡና ነው?
9. በአክብሮት በአሳብ ዙሪያ የመነጋገር ባህል እንዴት እናዳብር? ጥያቄ ያነሳን ማውገዝ እስከ መቸ ይቀጥል?
10. ፓስተር ዳንኤል የጠቀሷቸው "ሐዋርያ ነን ነቢያት ነን" የሚሉ፣ ለገዥው መንግሥት (ለጠ/ሚንስትሮች መለስ ዜናዊ፣ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ዐቢይ አሕመድ ተንባዮች፣ ከቤተ መንግሥት ደጅ እና ጓዳ የማይጠፉ መሆናቸው እንዴት ይታይ? ወጣቱን ስለሚያስተባብሩላቸው፣ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ስለሚያስገኙላቸው፣ ፍትኅ አልበኝነታቸውን በትንቢት ስለሚያደበዝዙላቸው፣
"ሐዋርያቱ ነቢያቱ" ምን ያህል ሕዝብ ቢያራቁቱ ሚንስትሮቹ ይጠቀሙባቸዋል እንጂ አያስቆሟቸውም። ለዚህ መፍትሔው ምንድነው? የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ጌታ እና አዳኝ ለሆነው ለኢየሱስ እንጂ ለዓለማዊ ሥልጣን ንዋይ ዝና መንበርከኳ እንዴት ያብቃ?
~ ምትኩ አዲሱ

Comments
Post a Comment