ተኪኒ ዶሮ እንደ ጣዖስ
ተኪኒ ዶሮ እንደ ጣዖስ
ተኪኒ ዶሮ፦ ወይ ዶሮ አልሆንኩ ወይ ጆፌ አሞራ፤ ይህን እርድ የመሰለ አንገቴን እንደ ተዋበች ስካርፍ ልሠርበት ወይስ ምን ላድርገው? አለ። ከዘመድ አዝማድ የለየኝ ሰንካላ ዕድሌ! አለ።
አንድ ቀን ከሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በስተ ጀርባ ከግራር ዛፍ ሥር ቊጭ ብሎ ይህንኑ ሲያሰላስል፣ አንድ ራእይ አየ። በራእዩ ውስጥ ያየው ፍጡር እርሱኑ ይመስላል፤ ግን ደግሞ እርሱን አይመስልም። ዐይኔ ነው? ምንድነው? አለ። እንደ ጧት ጮራ በመንግሥተ ሰማይ ፀዳል አሸብርቆ ከቊጥቋጦ ጀርባ ብቅ አለ። አጃቢ እንዳስከተለ ሙሽራ በሺህ ዐይኖች ተከብቧል። ገና ሲያየው የተኪኒ ልቡ ትርክክ አለ። እንዳይሸሽ እግሮቹ በመገረም ተሳሰሩ፤ ድረሱልኝ ብሎ እንዳይጣራ ድምጾቹ ጒሮሮው ውስጥ ተሠነጠሩ።
ፍጡሩ እየቀረበ መጣ። አከላቱ፣ ባይኑ ፊት ተስፋፍቶ የኅብረ ቀለማት መጋረጃ መሰለ፤ ቀረበ። ቆም አለ። ቆም ብሎ፣ ጣዖስ እባላለሁ! ስላንተ ወሬ ሰምቻለሁ አለ።
ተኪኒ ዶሮ ነፍስ አልቀረለትም፤ ከዚያን ቀን ጀምሮ ጣዖስ ለመሆን ብርቱ ምኞት አደረበት። ማልዶ ወንዝ ዳር ቆሞ የገዛ ፊቱን እያየ፤ የጣዖስን አካሄድና ቅላጼ መለማመድ ጀመረ።
አንድ ቀን ከወንዝ ዳርቻ ሲመለስ፣ በራእይ ያየውን ጌጣጌጥ ሜዳ ላይ ተበትነው አገኛቸው። ሚካኤል የልቤን ጸሎት ሰምቶ ዘረገፈልኝ አለ። ልክ እንዳየው አስተካክሎ ከበስተ ኋላው ጌጦቹን ጎንጉኖ አሠራቸው። ወደ ሠፈር ተመልሶ መጣ። ያዩ ሁሉ ምን ጒድ ነው! አሉ። የሰሙ ሊያዩ መጡ። ይኸ ከምድረ በዳ እንደ ደመና ዐምድ ተመዝዞ የወጣ ነው? የክዋክብት ስባሪ ከሰማይ ተምዘግዝጎ ወርዶ ነው! የጥበብና የውበት ቊንጮ እኛ ደቂቃን መሓል ምን ሊያደርግ መጣ? እግዚዖ! አሉ።
ከደመናው ውስጥ ግምግምታ ተሰማ፤ ብልጭልጭታ ታየ፤ ድንገት ዶፈ። ሁላቸውም ለመጠለል ሸሹ፣ ያቺን እለት ማ ማ እንደ ሆነ ተገለጠ።
© ምትኩ አዲሱ፣ ከ ፋቡላ ከንደገና፣ 2012 ዓም፤ ገጽ 56—57። ኮቪድ እስረኛ ባደረገን ዘመን የተፃፈ።
Comments
Post a Comment